፩ኛ ፡ ወደ ፡ ተሰሎንቄ ፡ ሰዎች - ምዕራፍ ፪ (1st Thesallonians - Chapter 2)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ ራሳችሁ ፡ ወደ ፡ እናንተ ፡ መግባታችን ፡ ከንቱ ፡ እንዳልሆነ ፡ ታውቃላችሁና። ፪፡ ነገር ፡ ግን ፡ እንደምታውቁት ፡ በፊልጵስዩስ ፡ አስቀድመን ፡ መከራ ፡ ተቀብለን ፡ ተንገላትተንም ፥ በብዙ ፡ ገድል ፡ የእግዚአብሔርን ፡ ወንጌል ፡ ለእናንተ ፡ እንናገር ፡ ዘንድ ፡ በአምላካችን ፡ ደፈርን። ፫፡ ልመናችን ፡ ከስሕተት ፡ ወይም ፡ ከርኵሰት ፡ ወይም ፡ ከተንኰል ፡ አልነበረምና ፤ ፬፡ ነገር ፡ ግን ፡ ወንጌልን ፡ አደራ ፡ ይሰጠን ፡ ዘንድ ፡ እግዚአብሔር ፡ የታመንን ፡ ሆነን ፡ እንዳገኘን ፡ መጠን ፥ እንዲሁ ፡ እንናገራለን ፥ ልባችንን ፡ የሚመረምር ፡ እግዚአብሔርን ፡ እንጂ ፡ ሰውን ፡ ደስ ፡ እንደምናሰኝ ፡ አይደለም። ፭፡ እንደምታውቁ ፥ እያቈላመጥን ፡ ከቶ ፡ አልተናገርንም ፥ እግዚአብሔርም ፡ እንደሚመሰክር ፡ እያመካኘን ፡ በመጐምጀት ፡ አልሠራንም ፤ ፮፡ የክርስቶስም ፡ ሐዋርያት ፡ እንደ ፡ መሆናችን ፡ ልንከብድባችሁ ፡ ስንችል ፥ ከእናንተ ፡ ቢሆን ፡ ወይም ፡ ከሌሎች ፡ ክብርን ፡ ከሰው ፡ አልፈለግንም። ፯፡ ነገር ፡ ግን ፡ ሞግዚት ፡ የራስዋን ፡ ልጆች ፡ እንደምትከባከብ ፥ በመካከላችሁ ፡ የዋሆች ፡ ሆንን ፤ ፰፡ እንዲሁም ፡ እያፈቀርናችሁ ፡ የእግዚአብሔርን ፡ ወንጌል ፡ ለማካፈል ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ የገዛ ፡ ነፍሳችንን ፡ ደግሞ ፡ እናካፍላችሁ ፡ ዘንድ ፡ በጎ ፡ ፈቃዳችን ፡ ነበረ ፥ ለእኛ ፡ የተወደዳችሁ ፡ ሆናችሁ ፡ ነበርና። ፱፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ ድካማችንና ፡ ጥረታችን ፡ ትዝ ፡ ይላችኋልና ፤ ከእናንተ ፡ በአንዱ ፡ ስንኳ ፡ እንዳንከብድበት ፡ ሌሊትና ፡ ቀን ፡ እየሠራን ፥ የእግዚአብሔርን ፡ ወንጌል ፡ ለእናንተ ፡ ሰበክን። ፲፡ በእናንተ ፡ በምታምኑ ፡ ዘንድ ፡ በእንዴት ፡ ያለ ፡ ቅድስናና ፡ ጽድቅ ፡ ነቀፋም ፡ በሌለበት ፡ ኑሮ ፡ እንደ ፡ ሄድን ፥ እናንተና ፡ እግዚአብሔር ፡ ምስክሮች ፡ ናችሁ ፤ ፲፩፡ ወደ ፡ መንግሥቱ ፡ ወደ ፡ ክብሩም ፡ ለጠራችሁ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ እንደሚገባ ፡ ትመላለሱ ፡ ዘንድ ፡ እየመከርንና ፡ እያጸናን ፡ እየመሰከርንላችሁም ፥ አባት ፡ ለልጆቹ ፡ እንደሚሆን ፡ ለእያንዳንዳችሁ ፡ እንደ ፡ ሆንን ፡ ታውቃላችሁና። ፲፪፡ ስለዚህም ፡ የመልእክትን ፡ ቃል ፡ እርሱም ፡ የእግዚአብሔር ፡ ቃል ፡ ከእኛ ፡ በተቀበላችሁ ፡ ጊዜ ፥ በእውነት ፡ እንዳለ ፡ በእናንተ ፡ በምታምኑ ፡ ደግሞ ፡ እንደሚሠራ ፡ እንደ ፡ እግዚአብሔር ፡ ቃል ፡ እንጂ ፡ እንደ ፡ ሰው ፡ ቃል ፡ አድርጋችሁ ፡ ስላልተቀበላችሁት ፥ እኛ ፡ ደግሞ ፡ እግዚአብሔርን ፡ ሳናቋርጥ ፡ እናመሰግናለን። ፲፫፡ እናንተ ፥ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ በይሁዳ ፡ የሚኖሩትን ፡ በክርስቶስ ፡ ኢየሱስ ፡ ያሉትን ፡ የእግዚአብሔርን ፡ ማኅበሮች ፡ የምትመስሉ ፡ ሆናችኋልና ፤ እነርሱ ፡ ከአይሁድ ፡ መከራ ፡ እንደ ፡ ተቀበሉ ፥ እናንተ ፡ ደግሞ ፡ ያንን ፡ መከራ ፡ ከአገራችሁ ፡ ሰዎች ፡ ተቀብላችኋልና። ፲፬፡ እነዚያም ፡ ጌታን ፡ ኢየሱስን ፡ ደግሞ ፡ ገደሉ ፡ ነቢያትንም ፡ እኛንም ፡ አሳደዱ ፥ እግዚአብሔርንም ፡ ደስ ፡ አያሰኙም ፥ ሰዎችንም ፡ ሁሉ ፡ ይቃወማሉ ፥ ፲፭፡ ሁልጊዜ ፡ ኃጢአታቸውን ፡ ይፈጽሙ ፡ ዘንድ ፡ አሕዛብ ፡ እንዲድኑ ፡ እንዳንናገራቸው ፡ ይከለክሉናልና። ነገር ፡ ግን ፡ ቍጣው ፡ ወደ ፡ እነርሱ ፡ ፈጽሞ ፡ ደርሶአል። ፲፮፡ እኛ ፡ ግን ፥ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ በልብ ፡ ያይደለ ፡ ፊት ፡ ለፊት ፡ ለጥቂት ፡ ጊዜ ፡ አጥተናችሁ ፥ በብዙ ፡ ናፍቆት ፡ ፊታችሁን ፡ ለማየት ፡ እጅግ ፡ ሞከርን ፤ ፲፯፡ ወደ ፡ እናንተ ፡ ልንመጣ ፡ ወደን ፡ ነበርና ፥ እኔ ፡ ጳውሎስም ፡ አንድና ፡ ሁለት ፡ ጊዜ ፥ ሰይጣን ፡ ግን ፡ አዘገየን። ፲፰፡ ተስፋችን ፡ ወይስ ፡ ደስታችን ፡ ወይስ ፡ የትምክህታችን ፡ አክሊል ፡ ማን ፡ ነው ? በጌታችን ፡ በኢየሱስ ፡ ፊት ፡ በመምጣቱ ፡ እናንተ ፡ አይደላችሁምን ? ፲፱፡ እናንተ ፡ ክብራችን ፡ ደስታችንም ፡ ናችሁና።












Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.