የለብኝ ፡ ኩነኔ (Yelebegn Kunenie) - ታምራት ፡ ሃይሌ

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ

 
ካህኑ ፡ ኢያሱ ፡ ቢቆሽሽም ፡ ልብሱ
ቢጠፋው ፡ ውበቱ ፡ ቢደክም ፡ ጉልበቱ
አምላኩ ፡ አልተወውም ፡ አልቆበት ፡ ምህረቱ
የጠላትን ፡ ምኞት ፡ አደረገበት ፡ ከንቱ
ሰይጣን ፡ ቢከሰውም ፡ እያብጠነጠነ
ሳር ፡ እየበተሰ ፡ ስር ፡ እየነቀለ

ከሳሽም ፡ እራሱ ፡ ምስክር ፡ እራሱ
ጌታ ፡ በቀባው ፡ ላይ ፡ ሲያስረዝም ፡ ምላሱን
የተሰየመውን ፡ ከችሎቱ ፡ መሃል
ቀና ፡ ብሎ ፡ ቢያየው ፡ የእርሱ ፡ አምላክ ፡ ኖሯል

እኔ ፡ አልፈርድበትም ፡ ይሂድ ፡ ወደ ፡ ቤቱ
ከስልጣኑ ፡ አይውረድ ፡ ይቀጥል ፡ ክህነቱ
ተቀብዬዋለሁ ፡ ከነ ፡ ማንነቱ
የጠላትን ፡ ምኞት ፡ አድርጊያለሁ ፡ ከንቱ

ያዳም ፡ ዘር ፡ አፈር ፡ ስጋ
ሰው ፡ መሆኑን ፡ ሳልዘነጋ
የጠራሁን ፡ በእኔ ፡ ጸጋ
ዋጋው ፡ አለ ፡ ከእኔው ፡ ጋር

ይልቅ ፡ እድፋሙን ፡ ልብስ ፡ አውልቁለት ፡ ቶሎ
መሸማቀቁ ፡ ይቅር ፡ ይሂድ ፡ ቀና ፡ ብሎ
የክት ፡ ልብስ ፡ ይልበስ ፡ ከእግር ፡ እስከራሱ
ከእንግዲህ ፡ ነጻ ፡ ነው ፡ ተፈቷል ፡ ኢያሱ

አዝ:- በክርስቶስ ፡ ኢየሱስ ፡ ስራ ፡ በማመኔ
የለብኝ ፤ የለብኝ ፤ የለብኝ ፡ ኩነኔ (፪x)

ቃሉ ፡ እንደሚናገር ፡ ጥንት ፡ በዖፅ ፡ አገር
ኢዮብ ፡ የተባለ ፡ አንድ ፡ ሰው ፡ ነበር
ፍፁምና ፡ ቅን ፡ ነው ፡ ከክፋት ፡ የራቀ
አምላኩን ፡ ሚፈራ ፡ አመጽ ፡ ያላወቀ
በልጅና ፡ በሃብት ፡ መባረኩን ፡ አይቶ
ያሳጣው ፡ ጀመረ ፡ ቀናተኛው ፡ ቀንቶ

ክሱን ፡ አዘነበው ፡ በራሱ ፡ እየማለ
ስለባረከው ፡ ነው ፡ የፈራህ ፡ እያለ
እስቲ ፡ የዙሪያውን ፡ አጥሩን ፡ አፍርስበት
እጅህን ፡ ዘርጋና ፡ ያለውን ፡ ንካበት
ያኔ ፡ ይሰድብሃል ፡ አንደበቱን ፡ ከፍቶ
ማነው ፡ የሚታገስ ፡ ሃብቱን ፡ ተቀምቶ
እያለ ፡ ቢከሰው ፡ ሃሰትን ፡ ቀምሞ
ኢዮብ ፡ ድል ፡ አደረገ ፡ በእምነቱ ፡ ቆሞ

ወዶ ፡ ሰጠኝ ፡ እግዚአብሔር ፡ ለምሥጋናው ፡ ለእርሱ ፡ ክብር
ደግሞም ፡ ወዶ ፡ ከወሰደው ፡ አይጠየቅ ፡ ስልጣኑ ፡ ነው

መልካሙን ፡ እንዳየ ፡ ክፉን ፡ ብንቀበል
ሥሙ ፡ ብሩክ ፡ ይሁን ፡ ምሥጋናው ፡ ከፍ ፡ ይበል
ሁለት ፡ እጥፍ ፡ ክሶ ፡ እግዚአብሔር ፡ ፈረደ
ኢዮብ ፡ በድል ፡ ወጣ ፡ ከሳሽ ፡ ተዋረደ

አዝ:- በክርስቶስ ፡ ኢየሱስ ፡ ስራ ፡ በማመኔ
የለብኝ ፤ የለብኝ ፤ የለብኝ ፡ ኩነኔ (፪x)

እኔን ፡ ደስ ፡ ሲለኝ ፡ ጠላቴ ፡ ከፍቶታል
መባረኬን ፡ ሲያይ ፡ እሳት ፡ ሆኖበታል
ምክሩ ፡ ፈረሰበት ፡ አልሆነ ፡ እንዳሰበው
እኔም ፡ ድሌን ፡ ላውጅ ፡ ጨምሮ ፡ ያንገብግበው
መልካሙን ፡ ስራውን ፡ በእኔ ፡ የጀመረው
ይፈጽምልኛል ፡ ጌታዬ ፡ ታማኝ ፡ ነው

ሰይጣን ፡ ዘዋሪ ፡ ነው ፡ ሁሉን ፡ ያዳርሳል
መክሰስ ፡ ልማዱ ፡ ነው ፡ ማንንም ፡ ይከሳል
የክርስቶስን ፡ ደም ፡ ዋጋ ፡ አሳንሶ
ከወንጌሉ ፡ ተስፋ ፡ ግማሹን ፡ ቀንሶ
በተንኮል ፡ ሽንገላው ፡ እይተታለልን
ሶኮነን ፡ ሲከሰስ ፡ ስንቱ ፡ ከቤት ፡ ዋለ
ዘወትር ፡ የሚሸከም ፡ ጉድለት ፡ ድካምህን
በሰማያት ፡ አለ ፡ ታላቅ ፡ ሊቀ ፡ ካህን

እኔም ፡ ሆንኩኝ ፡ አንተም ፡ አንቺ
ለሰይጣን ፡ ክስ ፡ አትመቺ
አለንና ፡ ዋስ ፡ ጠበቃ
ለሁላችን ፡ የሚበቃ

ከእምነት ፡ አናፈግፍግ ፡ እንታመን ፡ እንጂ
አለን ፡ በሰማያት ፡ ጽድቅ ፡ አማላጅ
ሙሉ ፡ ዋጋ ፡ ከፍሎ ፡ በጸጋው ፡ አድኖኛል
ሁሉን ፡ አሳልፎ ፡ ጽዮን ፡ ያገባኛል

አዝ:- በክርስቶስ ፡ ኢየሱስ ፡ ስራ ፡ በማመኔ
የለብኝ ፤ የለብኝ ፤ የለብኝ ፡ ኩነኔ (፪x)