From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
በእርጅና ፡ የወለድኩት ፡ ልጄ ፡ ሞቶብኛል
አጥንቱን ፡ ሳያስቀር ፡ አውሬ ፡ በልቶብኛል
ወደ ፡ ሙታን ፡ ስፍራ ፡ እያዘንኩ ፡ እወርዳለሁ
ስለ ፡ ዮሴፍ ፡ ልጄ ፡ ዝምብዬ ፡ አለቅሳለሁ
ከልጆቼ ፡ ሁሉ ፡ ይልቅ ፡ እወደው ፡ ነበር
ቀሚስ ፡ ገዝቼለት ፡ ያጌጠች ፡ በህብል
አስተዋዩ ፡ ልጄ ፡ ዮሴፍ ፡ ዛሬ ፡ ጠፍቷል
ከልብሱ ፡ በስተቀር ፡ ሥጋው ፡ ተቦጫጭቋል
እነዛ ፡ ሁለት ፡ ህልሞቹን ፡ ስጠብቅ ፡ ነበር
ልጄን ፡ ትልቅ ፡ ቦታ ፡ እንዳየው ፡ ሲከብር
ዛሬ ፡ የልጄን ፡ መርዶ ፡ ሰምቼ ፡ አዝኛለሁ
ሰዎች ፡ ቢያጽናኑኝስ ፡ እንዴት ፡ አጽናናለሁ
ይልጆቼን ፡ ወሬ ፡ አምጣልኝ ፡ ብዬ
እኔው ፡ ነኝ ፡ ያዘዝኩት ፡ በበረሃ ፡ ልጄ
እራሴው ፡ ነኝ ፡ እኔው ፡ አውሬ ፡ ያስበላሁት
የሕይወቱን ፡ ጽዋ ፡ በአንዴ ፡ ያስጨለጥኩት
ኧረ ፡ ምነው ፡ ቢቀርብኝ ፡ ባይላክስ ፡ ኖሮ
ደህና ፡ አየው ፡ ነበረ ፡ ዮሴፍ ፡ በእድሜው ፡ ከብሮ
እናቱም ፡ ወንድሙን ፡ ስታምጥ ፡ ሞታለች
ይህንንማ ፡ ብታይ ፡ ምንስ ፡ ትለኛለች
እያለ ፡ ሲናገር ፡ ያዕቆብ ፡ በጣም ፡ አዝኖ
በልጁ ፡ ዮሴፍ ፡ ሞት ፡ እጅግ ፡ ተጸጽቶ
ልጁን ፡ የሚታደግ ፡ እግዚአብሔር ፡ አለና
ዮሴፍ ፡ በሕይወት ፡ አለ ፡ ምስራች ፡ ተሰማ
አዝ፦ እግዚአብሔር ፡ ታድጐታልና
ዮሴፍ ፡ በሕይወት ፡ አለ ፡ እንደገና (፪x)
ሞተ ፡ ብለው ፡ አረዱት ፡ የምስራች ፡ አሉ
ቃሉ ፡ ተፈጸመ ፡ ለዮሴፍ ፡ ሰገዱ
የዮሴፍ ፡ ወንድሞች ፡ ዮሴፍን ፡ ሸጠዋል
ግን ፡ ጌታ ፡ አክብሮት ፡ ሻጩን ፡ ያሰግዳል
አዝ፦ እግዚአብሔር ፡ ዮሴፍን ፡ ወዶታል
በወንድሞቹ ፡ ላይ ፡ አክብሮታል (፪x)
ያዕቆብ ፡ የእንባው ፡ ዘመን ፡ ዛሬ ፡ አበቃለት
የዕድሜውም ፡ ፍጻሜ ፡ እልልታ ፡ ሆነለት
የሃያ ፡ ብር ፡ ባሪያ ፡ ዛሬ ፡ ጌታ ፡ ሆኗል
በምድረ ፡ ግብጽ ፡ ውስጥ ፡ ንጉሥ ፡ አክብሮታል
አዝ፦ እግዚአብሔር ፡ ዮሴፍን ፡ ወዶታል
በምድር ፡ ሁሉ ፡ ዙሪያ ፡ አክብሮታል
እግዚአብሔር ፡ ታድጐታልና
ዮሴፍ ፡ በሕይወት ፡ አለ ፡ እንደገና
እግዚአብሔር ፡ ታድጐኛልና
እኔም ፡ በሕይወት ፡ አለሁ ፡ እንደገና (፪x)
እግዚአብሔር ፡ ታድጐሃልና
አንተም ፡ በሕይወት ፡ አለህ ፡ እንደገና
እግዚአብሔር ፡ ታድጐሻልና
አንቺም ፡ በሕይወት ፡ አለሽ ፡ እንደገና
እግዚአብሔር ፡ ታድጐናልና
እኛም ፡ በሕይወት ፡ አለን ፡ እንደገና(፪x)
|