የያዕቆብ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፭ (James - Chapter 5)

From WikiMezmur, the free amharic mezmur lyrics database.
ዘልለው ለመሔድ፦ የማውጫ ቁልፎች, ፍለጋ


፩፡ አሁንም ፡ እናንተ ፡ ባለ ፡ ጠጎች ፥ ስለሚደርስባችሁ ፡ ጭንቅ ፡ ዋይ ፡ ዋይ ፡ እያላችሁ ፡ አልቅሱ። ፪፡ ሀብታችሁ ፡ ተበላሽቶአል ፥ ልብሳችሁም ፡ በብል ፡ ተበልቶአል። ፫፡ ወርቃችሁም ፡ ብራችሁም ፡ ዝጎአል ፥ ዝገቱም ፡ ምስክር ፡ ይሆንባችኋል ፡ ሥጋችሁንም ፡ እንደ ፡ እሳት ፡ ይበላል። ለኋለኛው ፡ ቀን ፡ መዝገብን ፡ አከማችታችኋል። ፬፡ እነሆ ፥ እርሻችሁን ፡ ያጨዱት ፡ የሠራተኞች ፡ ደመወዝ ፡ በእናንተ ፡ ተቀምቶ ፡ ይጮኻል ፥ የአጫጆችም ፡ ድምፅ ፡ ወደ ፡ ጌታ ፡ ፀባዖት ፡ ጆሮ ፡ ገብቶአል። ፭፡ በምድር ፡ ላይ ፡ ተቀማጥላችኋል ፡ በሴሰኝነትም ፡ ኖራችኋል ፤ ለእርድ ፡ ቀን ፡ እንደሚያወፍር ፡ ልባችሁን ፡ አወፍራችኋል። ፮፡ ጻድቁን ፡ ኰንናችሁታል ፡ ገድላችሁትማል ፤ እናንተን ፡ አይቃወምም። ፯፡ እንግዲህ ፥ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ ጌታ ፡ እስኪመጣ ፡ ድረስ ፡ ታገሡ። እነሆ ፥ ገበሬው ፡ የፊተኛውንና ፡ የኋለኛውን ፡ ዝናብ ፡ እስኪቀበል ፡ ድረስ ፡ እርሱን ፡ እየታገሠ ፡ የከበረውን ፡ የመሬት ፡ ፍሬ ፡ ይጠብቃል። ፰፡ እናንተ ፡ ደግሞ ፡ ታገሡ ፥ ልባችሁንም ፡ አጽኑ ፤ የጌታ ፡ መምጣት ፡ ቀርቦአልና። ፱፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ እንዳይፈረድባችሁ ፡ እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ አታጉረምርሙ ፤ እነሆ ፥ ፈራጅ ፡ በደጅ ፡ ፊት ፡ ቆሞአል። ፲፡ ወንድሞች ፡ ሆይ ፥ የመከራና ፡ የትዕግሥት ፡ ምሳሌ ፡ የሆኑትን ፡ በጌታ ፡ ስም ፡ የተናገሩትን ፡ ነቢያትን ፡ ተመልከቱ። ፲፩፡ እነሆ ፥ በትዕግሥት ፡ የጸኑትን ፡ ብፁዓን ፡ እንላቸዋለን ፤ ኢዮብ ፡ እንደ ፡ ታገሠ ፡ ሰምታችኋል ፥ ጌታም ፡ እንደ ፡ ፈጸመለት ፡ አይታችኋል ፤ ጌታ ፡ እጅግ ፡ የሚምር ፡ የሚራራም ፡ ነውና። ፲፪፡ ከሁሉም ፡ በፊት ፥ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ በሰማይ ፡ ቢሆን ፡ በምድርም ፡ ቢሆን ፡ በሌላ ፡ መሐላም ፡ ቢሆን ፡ በምንም ፡ አትማሉ ፤ ነገር ፡ ግን ፡ ከፍርድ ፡ በታች ፡ እንዳትወድቁ ፡ ነገራችሁ ፡ አዎን ፡ ቢሆን ፡ አዎን ፡ ይሁን ፥ አይደለምም ፡ ቢሆን ፡ አይደለም ፡ ይሁን። ፲፫፡ ከእናንተ ፡ መከራን ፡ የሚቀበል ፡ ማንም ፡ ቢኖር ፡ እርሱ ፡ ይጸልይ ፤ ደስ ፡ የሚለውም ፡ ማንም ፡ ቢኖር ፡ እርሱ ፡ ይዘምር። ፲፬፡ ከእናንተ ፡ የታመመ ፡ ማንም ፡ ቢኖር ፡ የቤተ ፡ ክርስቲያንን ፡ ሽምግሌዎች ፡ ወደ ፡ እርሱ ፡ ይጥራ ፤ በጌታም ፡ ስም ፡ እርሱን ፡ ዘይት ፡ ቀብተው ፡ ይጸልዩለት። ፲፭፡ የእምነትም ፡ ጸሎት ፡ ድውዩን ፡ ያድናል ፡ ጌታም ፡ ያስነሣዋል ፤ ኃጢአትንም ፡ ሠርቶ ፡ እንደ ፡ ሆነ ፡ ይሰረይለታል። ፲፮፡ እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ በኃጢአታችሁ ፡ ተናዘዙ። ትፈወሱም ፡ ዘንድ ፡ እያንዳንዱ ፡ ስለ ፡ ሌላው ፡ ይጸልይ ፤ የጻድቅ ፡ ሰው ፡ ጸሎት ፡ በሥራዋ ፡ እጅግ ፡ ኃይል ፡ ታደርጋለች። ፲፯፡ ኤልያስ ፡ እንደ ፡ እኛ ፡ የሆነ ፡ ሰው ፡ ነበረ ፥ ዝናብም ፡ እንዳይዘንብ ፡ አጥብቆ ፡ ጸለየ ፥ በምድርም ፡ ላይ ፡ ሦስት ፡ ዓመት ፡ ከስድስት ፡ ወር ፡ አልዘነበም ፤ ሁለተኛም ፡ ጸለየ ፥ ፲፰፡ ሰማዩም ፡ ዝናብን ፡ ሰጠ ፡ ምድሪቱም ፡ ፍሬዋን ፡ አበቀለች። ፲፱፡ ወንድሞቼ ፡ ሆይ ፥ ከእናንተ ፡ ማንም ፡ ከእውነት ፡ ቢስት ፡ አንዱም ፡ ቢመልሰው ፥ ፳፡ ኃጢአተኛን ፡ ከተሳሳተበት ፡ መንገድ ፡ የሚመልሰው ፡ ነፍሱን ፡ ከሞት ፡ እንዲያድን ፥ የኃጢአትንም ፡ ብዛት ፡ እንዲሸፍን ፡ ይወቅ።












Navigation menu

MediaWiki spam blocked by CleanTalk.